ሃገራችን ያለችበትን ሁኔታ እና የግል አስተያየቴን ይመለከታል

Berhane Kidanemariam
4 min readMar 10, 2021

በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለማበርከት ጥረት አድርጌአለሁ ። ህዝቤን እና ሃገሬን ለማገልገል ህግና ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት በንፁህ ህሊና ተንቀሳቅሻለሁ ። በአስተዳደር በሚዲያ ስራ አመራርና እንደዚሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተለይ በሃገረ አሜሪካ ግዛት ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል እንደዚሁም በአሁኑ ሰዓት በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የሚሲዮኑ ምክትል መሪ በመሆን በማገልገል ላይ እገኛለሁ ።

ብልፅግናን ጨምሮ በየትኛውም ፓርቲ አባል እንዳልሆኩ የሚታወቅ ሲሆን ይህ የሆነውም ቀድም ባሉ ዓመታት በነበረኝ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና የአመለካከት ልዩነት ምክንያት በመገለሌ ነው። ይሁን እና በአገኘሁት መድረክ ከማገኛቸው የመንግስት እና ፓርቲ ባለስልጣናት ሃገሬን እና ህዝቤን በተመለከተ በመወያየት፤ ጭንቀቴንና ሃሳቤን ሳላካፍል ያለፍኩበት አጋጣሚ አልነበረም።

ከበፊት ጀምሮ ሲያሳስበኝ የነበረው እና በየአጋጣሚው ሳነሳ የቆየሁት አገራችን ውስጥ ስለተከሰተው ለውጥና ሂደት በተመለከተ ይኽውም ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እና አስጫናቂ እየሆነ መምጣቱ የአገር ህልውና እና ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ እንቅልፍ እና እረፍት የሚነሳ ነበር። ሁላችንም እንደምናስታውሰው ለውጡ በተለይም በአገራዊ ፖለቲካ መግባባት ዙሪያ እንዲሁም ዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ለማስፋን ጥረት ማድረግን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ያካተተ ሁሉንተናዊ ሪፎም የጠበቀን ቢሆንም ሂደቱ እና ውጤቱ ሁሉም ከጠበቀው በተቃራኒው እየሆነ ፤ ያለማቋረጥ መፈናቀል ፤ እስር፤ ግድያ፤ ጦርነት ፤ ደም መፋሰስ፤ የዕለት ተዕለት ተሞክሮአችን ሆኖ ቆይቷል።

ችግሮችን በውይይት በድርድር እና በሰላም ከመፍታት ይልቅ የመንግስትን አቅም በመጠቀም ሁሉንም በጉልበት የመፍታት አካሄድ የተለመደ ሆኗል።

ኦሮሚያ ላይ ሲካሄድ የቆየው ድብቅ ጦርነት ፤ ቤንሻንጉል ላይ ያለው ደም መፋሰስ ፤ ደቡብ ክልል ውስጥ ያለው መፈናቀል ፤ ግድያ እና እስራት ፤ አዲስ አበባ ላይ ባሉት ጋዜጠኞች ላይ ሳይቀር የዘፈቀደ እስር እና ወከባ እንዲሁም ማንነት ላይ ያተኮረ ማግለልና ማስፈራራት — — — ወዘተ የስርዓቱ ምንነት መገለጫ ሆነዋል። በአጠቃላይ የተጠበቀው ለውጥ እና እሱን ተከትሎ እየታዩ ያሉት አስጨናቂ ሁኔታዎች ዲሞክራሲ እና ልማት ማሰብ ቀርቶ ፤ በሰላም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ራሱ አስፈሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በህዝባችን ማሀል ሊሰነቀር እየታሰበ ያለው አለመተማመን ፤ ጭራሽ እንደ ህዝብ እንደ ሃገር የመቀጠላችን ነገር አሳሳቢ ያደርገዋል። ለውጡን ተከትሎ በዜጎች እና በትላልቅ ባለስልጣናት የተፈፀሙት ግድያዎች ስናስታውስ ታዋቂው ኢንጅነር ስመኘው ፤ ጀነራል ሰዓረ ፤ ጀነራል ገዛኢ ፤ ዶ/ር አምባቸው እና የካብኔው አባላቶች ፤ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ፤ እሱን ተከትሎ የመጣው የነ አቶ ጀዋር ፤ የአቶ በቀለ ገርባ እና ደጋፊዎቻቸው የእነ እስክንድር ነጋ ፤ የአቶ ልደቱ እና ኢንጅነር ይልቃል እስር እና የፍርድ ሂደት አገራችን እየሄድችበት ያለው የቁልቁለት መንገድ ተንደርድረን የት እንደምንገባ ከወዲሁ ግልፅ ያደርገዋል።

ከዚህም አልፎ ከአማራ ክልል የመጡ እና ወደ ቤተሰቦቻቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ ተሰውረው የቀሩ እህቶቻችን ስናስብ የነገ ተስፋችን እና ህልውናችን ጭለማ ያደርገዋል ። በድምሩ ስንመዝነው እነዚህ ተከታታይ ፍፃሜዎች በማን እና በምን ምክንያት እንደተፈፀሙ ሳይታወቅ ሁሉም እንደተድበሰበሰ እና በድብቅ እንደተያዘ ያለ መፍትሔ እዚህ ደረጃ ደርሰናል። የዚህ ሁሉ መሰረታዊ ምክንያት የስርዓቱ አምባገነን መሆንና በህዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የመጣ ለውጥ ባለመሆኑ ፤ አካታች እና አሳታፊ ያለመሆኑ ተጠቃሽ ምክንያት ነው።በውይይት በድርድር በሰጥቶ መቀበል የማያምን አስተሳሰብ እና ቡድን እስካለ ድረስ የችግሩ መቀጠል እና የአገራችን ህልውና ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድም ብሎም የአለምን ሰላም ጠንቅ ሊሆን የሚችል ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ ከማንም ጊዜ በላይ በበለጠ ግልፅ የሆነበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው።

የዚህ ስርዓት የለየለት አምባገነን መሆን በትግራይ ላይ የተከፈተው ጦርነት የበለጠ ግልፅ ያደርገዋል። ይኽውም ለረዥም ጊዜ ሲደረግ የነበረው የጦርነት ዝግጅት እና እሱን ዳር ለማድረስ ሲከናወን የነበረው ተከታታይነት ያለው የፖለቲካ እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በተለይ የኤርትራን እና የሶማልያን ፤ የኤምሬቶች ቴክኖሎጂና የጦርነት ተሳትፎ ጉልህ ማሳያዎች ናቸው።

የራሱን ህዝብ ከጠላት ሃገር ሰራዊት በመተባበር የሃገሩን መሰረተ ልማት የጤና የትምህርት የመንገድ በአጠቃላይ ሁሉንም የሰው ሃይል ሳይቀር ለመፍጀት መረባረቡ አለም በግልፅ የመሰከረለት በምንም አይነት መንገድ መደበቅ ያልተቻለ የጦር ወንጀል መፈፀሙ ገሃድ ነው።

ሁሉም የእምነት ተቋማት ማፍረስ እና ማራከስ ሴት እህቶቻችንን መድፈር የምግብ እና ለሰው ልጅ አስፈላጊ የተባሉትን ነገሮች ተደራሽ እንዳይሆን ሆን ተብሎ መከልከል እና ማስራብ ዓለም እንዳይሰማው እንዳያየው ሚዲያን በመከልከል በድቅድቅ ጨለማ ህዝብን እየፈጁ ታላቅ ጀግንነት እንደተፈፀመ በማስመሰል በአጉል ፕሮፖጋንዳ ህዝብን ማደናገር እና ማታለል እንደ ትልቅ ስኬት የሚነገር ነገር ግን እጅግ ኋላቀርና በዚህ ዘመን ሊፈፀም ይችላል ተብሎ የማይገመት ዝርፊያ ሁሉ የተካሄደበት ጦርነትና የዘር ፍጅት ነው።

ይህ ጦርነት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢ ያሉትን የዲሞክራሲ፤ የሰብዓዊ መብትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለማዳፈን በማስፈራሪያነት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በሌላ መልኩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የረዥም ዘመን አብሮነት መፈቃቀርም እንዲዳከም አገሪቱ እና ህዝቦቿ አንዱ በሌላው እንዲጠራጠር እና እንዲፈራራ ፤ የአንዱ መበደል ለሌላው ደስታው ሆኖ እንዲሰማው ሁሉ ጥረት ተደርጓል። በተለይ ፅንፈኝነትን በመሳሪያነት ጥቅም ላይ እንዲውል ሆን ተብሎ የህዝቦችን መልካም ግንኙነት እንዲፋለስ ተደርጓል። የኦሮሞ እና የአማራው ፤ የትግራይ እና የአማራው፤ ከዚያም አልፎ የኤርትራው ህዝብ ከትግራይ ህዝብ እስከ ወዲያኛው ለማለያየት በሚዲያ ጭምር ሌት ተቀን ተሰርቶበታል። ለዚህ ሲባል በርካታ በጀት ተመድቦ ሃገርን በማፍረስ እና ለማዳከም ጥቅም ላይ ውሏል። አስገራሚው ነገር ይህንን ወንጀል ለመፈፀም “የኢትዮጵያ አትፈርስም” አደናጋሪ ቃላት እንደ ዋና የግቡ ማሳኪያ ስልት ሆኖ ተሰርቶበታል ። በዚህ አስከፊ ጦርነት የሃገራችን ኢኮኖሚ እና አምራች ሃይል ከማውደም አልፈው ህዝባችን እርስ በእርስ እንዲጠራጠር እና የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ቀንድ ዋና አተራማሽ እና የለየለት አምባገነን የኤርትሪያው ቡድን እንዲጠናከር አካባቢያችን ሰላም እንዲርቀው ከማድረግ ውጭ ምንም የፈየደው ነገር የለም።

በዚህ ጦርነት የተፈፀመው የጦር ወንጀሎችን ለመሸፋፈን እና ከደሙ ንፁህ ነን ከማለት አልፎ ስማችን ጠፍቷል በማለት ሌላ መደበቂያ ስልት እና ፕሮፓጋንዳ የኢትዮጵያ አትፈርስም ተራ ሸንገላ በመጠቀም ሃቁን በሻቱ ሚዲያዎችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማትና ግለሰቦች እየወረደ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ፤ ማስፈራራት በተለይ ስም እየጠቀሱ ገንዘብ ተከፋይ ፤ ውሸታም እያሉ ማጠልሸት ዋነኛ የጥፋቱ መደበቂያ ስልት ሆኗል።

ህዝባችን እርስ በእርሱ እንዲለያይ እንዲራራቅ በዋንኛ የችግሩ ምንጭና መፍትሄ ላይ እንዳያተኩር ሆን ተብሎ እየተሰራበት ነው። ይህ ደግሞ የሃገራችን የኢትዮጵያ ህልውና ደህንነት እድገቷ እና ልማቷ እውን እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ህልውናዋን እንድጣትም ጭምር እየተደረገ ነው። በትግራይ በተጋሩ እየተፈፀመ ያለው በደል የዚህ ማሳያ ተግባር ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም ። እየተፈፀመ ያለው በደል ቃላት ከሚገልፁት በላይ ነው። ስለሆነም ይህን ሃገር እና ህዝብን የማፍረስ ተልዕኮ ያለው ተግባር የመቃወም ግዴታ አለብኝ ብዬ አምናለሁ ። ጭቆናን እና በደልን መቃወም ደግሞ የመጀመሪያዬ አይደለም ። ሁሌም ቢሆን ጭቆናን እና ግፍን ስቃወም ነበር። አሁንም እቀጥላለሁ ። አገሬ እና ህዝቤ ይህንን ሁሉ በደል እየደረሰበት እያየሁ እንዳላየሁ እንዳልሰማሁ ዝም ማለት አልችልም ። መናገር አለብኝ ብዬ አምናለሁ ። ግፍ ሞልቶ ፈሷልና። የዘር ፍጅት መቆም መቻል አለበት ።

በመንግስት መስሪያ ቤት ፤ በግሉ ዘርፍ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ተሰማርተው ሃገርና ወገንን በማገልገል ላይ ባሉ ወገኖች እና ዜጎች ማንነትን መሰረት ያደረገ የማጥላላት እና የማግለል ዘመቻ ካልቆመ የችግሩ መባባስ ውጤት አደገኛ እንደሚሆን መታወቅ አለበት። ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህንን አገር የማዳከም እና የማፍረስ አካሄድ በፅኑ ሊቃወመው ይገባል ።

በመጨረሻም የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት፤ ታዋቂ ግለሰቦች ፤ ሚዲያዎች ፤ መንግስታት በተለይ የዩኤስ አሜሪካ እና ለአውሮፓ ህብረት እየወሰዱ ያሉት እርምጃዎች እያደነቅሁ ኢትዮጵያን ለማዳን ችግሩን በፈጠረው አካል መፍትሔ ይገኛል ተብሎ ስለማይታሰብ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ተለቀው ሁሉንም ያካተተ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያሳትፍ የውይይት እና የሽግግር መድረክ እንዲዘጋጅ እና በግሌ ይህንን በሰላማዊ ህዝባችን እና በአጠቃላይ በአገራችን እየተፈፀመ ባለው ጥፋት ተሳታፊ ላለመሆን በገዛ ፋቃዴ ራሴን ከመንግሥት ስራ አግልያለሁ።

ብርሃነ ኪ/ማርያም

--

--